Thread 1
ኢትዮጵያና ወደብ፣
ብዙዎች ለኢትዮጵያ የባህር በር ተፈጥሮአዊ መብት መሆኑንና አለመሆኑን ሙግት ይገጥማሉ። የዚህ ቅጥልጥል አላማ ሙግቱን የመዳኘት ሳይሆን ፣ በኢትዮጵያ ወደብ አጠቃቀም ዙርያ አስገራሚና የተሸፈኑ እውነታዎችን ለማጫወት ነው
Thread 2
አዱሊስ፣
የወደብ ጥቅም በተደራጀ መልኩ በዛሬዋ ሀገራችን ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው በአክሱማዊያን ነው። አክሱማዊያንና ከነሱም በፊት የነበሩት የዳማት ልዑላን በአዱሊስ መጠቀምን የመረጡት በወቅቱ ገናና በነበሩ ግሪካዊያንና ባዛንታይን..
Thread 3
..ነገስታት ለመገናኘትና የእጣን፣የወርቅ ፣የከበሩ ድንጋዮች፣ የአደን ዱር አራዊት ቆዳ ምርቶቻቸውን ከነዚሁ ነገስታት ጋር ለመገበያየት ቅርበቱ ያመቻቸው ስለነበረ ነው።
"አዱሊስ" (Άδουλις)የሚለው ቃል ሳይቀር የአካባቢው ሳይሆን ግሪካዊ ነው
Thread 4
አዱሊስን መጀመርያ የጠቀሰው "ፕላይኒ ትልቁ" (Pliny The Elder) 'አብይ ገበያ ለትሮግሎዳይትና ለኢትዮጵያ ህዝቦች ገላጭ ለቀይ ባህርና ለህንድ ውቅያኖስ (principal mart for Troglodytae & the people of Aethiopia', guide of the Red Sea and the Indian Ocean)
Thread 5
..በእርግጥ አንዳንድ የታሪክ ተመራማሪዎች ፕላይኒ ትልቁ "ኢትዮጵያ" (Aethiopia) ያለው መላውን አፍሪካ ነው ብለው ሲከራከሩ ሌሎች "የለም ፣ ኢትዮጵያ ማለቱ አክሱማውያንን ነው" ብለው ይሞግታሉ። የሆነው ሆኖ የዚህ ጸሐፊ መዝገብ ለአዱሊስ ታሪክ
Thread 6
..እንደዋና የተሟላ ማጣቀሻ ተደርጎ ይታያል።
በዚሁ ጽሑፍ ፕላይኒ ትልቁ ፣ የዳማት ልዑላንና አክሱማዊ ነግስታት ከግሪክና ሮም በሚያደርጉት ንግድ እጅግ እንደከበሩና መንግስታቸውንም ገናና ያደረጉት በዚያ ገቢ እንደሆነ በጥልቀት ጽፏል።
Thread 7
..የአዱሊስ ወደብ እስከ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን በጥቅም ላይ ሲውል ቆይቶ ከኦቶማን ቱርኮች አካባቢውን መቆጣጠር ጋር ተያይዞ እስከእነ አካቴው ተትቶ ፣ በአሁኑ ወቅት በመሬት (inland) ተሸፍኖ ከባህር ርቆ ፍርስራሹ ይታያል።
Thread 8
ምጽዋ (ባፅእ)
..ከ8ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ በአካባቢው ቀስ በቀስ ስር የሰደደው የኦቶማን ቱርክ ገዛዔ-ኩሉሽ (Empire) ለግዛት ቅኝት ምቹ ቦታን በጥንቃቄ መርጦ የመስፈር ብልሀት ያለው በመሆኑ በጊዜው አነስተኛ መንደር በነበረችው ምጽዋ ሰፈረ።
Thread 9
በአካባቢው ይኖሩ የነበሩት የቤጃ ህዝቦች በመንደሪቱ አነስተኛ የከተማ መንግስት (city state) አቋቁመው ቀደም ብሎ ከአክሱም ከዚያ በሁዋላ ከአዲስ መጤዎቹ ተርኮች ጋር የገበያ ልውውጥ ያደርጉ ነበር። ይሁንና ከቱርኮች እየተጠናከሩ መምጣት ጋር
Thread 10
..ተያይዞ የከተማ መንግስታቸው አደጋ ላይ ወደቀ። ከተለያዮ በአቅራቢያው ከሚገኙ ቃታ፣ባቅሊን እና ዳህላክ ከሚባሉ አነስተኛ ጎሳዎች ጋር ህብረት በመፍጠር ህልውናቸውን ለማስጠበቅ ቢሞክሩም እጅግ ግዙፍና ዘመናዊ የነበረውን የኦቶማን ቱርክን
Thread 11
..ኃይል መቋቋም ስላቃታቸው ትንሿ የባህር ዳርቻ መንደራቸው ከቁጥጥራቸው ውጭ ወጣች። ኦቶማኖች ሙሉ በሙሉ አካባቢውን ከተቆጣጠሩ በሁዋላ ምጽዋን የተቀሙበት ባብዛኛው የደቡባዊ ቀይባህርን እንደ ቅኝት መቃኛ እንጂ ለወደብነት አልነበረም።
Thread 12
ይሁንና ከአክሱም መዳከም በሁዋላ በዛሬው ሰሜናዊ ኢትዮጵያ የተቋቋሙት መንግስታት ታላቁን የዛግዌ ስርወ መንግስት ንጉስ ላሊበላን (ገብረመስቀል) ጨምሮ የምጽዋን ወደብነት እንደሚፈልጉት ስለተገነዘቡ እንደ የተለያዩ ፓለቲካውና ሃይማኖታዊ
Thread 13
ፍላጎታቸው መያዣና ማስገደጃነት መጠቀም ጀመሩ። ለምሳሌ ንጉስ ላሊበላ ወደ ኢየሩሳሌም እንደልብ መመላለስ ህልም በዚሁ ምክንያት እክል ስለገጠመው ነበር አዲሲቱን ኢየሩሳሌም በኢትዮጵያ ለመገንባት የሻተውና የላሊበላን አብያተ ክርስቲያናት
Thread 14
..የገነባው ብለው በርካታ ታሪክ ጸሐፊዎች ጽፈዋል። ኦቶማን ቱርኮች ምጽዋና አካባቢውን እንደ ጦር ካምፕና ወደሌላው የቀይ ባህርና ህንድ ውቅያኖስ የሚያዘምቱት ወታደር መመልመያ ይጠቀሙበት ስለነበር በርካታ ህንጻዎችን ገንብተዋል።
Thread 15
ዘይላና በርበራ
..በኦቶማን ቱርክ እንቅፋት የተፈጠረባቸው የኢትዮጵያ ነገስታት ፊታቸውን ወደ ህንድ ውቅያኖሷ ዘይላ ወደብ አዞሩ። ምንም እንኳን የህንድ ውቅያኖስም በኦቶማን ቱርኮች ተጽእኖ ስር እየወደቀ ቢሆንም በአካባቢው አስቸጋሪ በሆነ
Thread 16
..ሁኔታ እንኳን ንግድን የማሳለጥ ከፍተኛ ችሎታ የነበራቸው የተለያዩ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው በመናገርና ራሳቸውን ከሚኖሩበት አካባቢ በማላመድ ተሰጥኦዋቸው የሚታወቁትን የአርጎባ ህዝቦችን በመጠቀም ዘይላን የኢትዮጵያ ዋና ወደብ አደረጉት
Thread 17
ይህንን የተገነዘቡት ኦቶማን ቱርኮች በተለያየ መንገድ ሞክረው ኢትዮጵያን በነሱ ሀይማኖታዊና ፖለቲካዊ ተጽእኖ ስር ለማሳደር የሚያደርጉትን ጥረት በመቀጠል በአካባቢው የነበሩትን የሶማሌ ባላባቶች የሀይማኖትና የጎሳ መሪዎችን
Thread 18
..በአርጎባ ነጋዴዎች ወደ መሐል ኢትዮጵያ የሚደረጉ የንግድ እንቅስቃሴዎችን እንዲያደናቅፉ ማበረታታት አልፎ አልፎም ማዘዝ አመጡ። እንግሊዛዊው ተጓዥ ጄምስ ብሩስ ስለኢትዮጵያ በጻፈው ታሪክ የግራኝ አህመድ ጦርነት ጥንስስ የጀመረው ያኔ..
Thread 19
..እንደነበር ጽፏል። የሆነው ሆነና በኦቶማን ቱርኮች የተከበበው የቀይ ባህርና የህንድ ውቅያኖስ ወደ የኢትዮጵያ መሪዎች የወደብ አገልግሎት በሚሹበት ጊዜ ሁሉ እንዲህ አይነት እንቅፋቶችን በመፍጠር ሀይላቸው እስከተዳከመበት እስከ 17ኛው
Thread 20
..ክፍለ ዘመን መጨረሻ ቆይተዋል። በዚህ ሁሉ ዘመን ከባህር ጠረፍ እቃዎችን በማመላለስና የባህር ንግድን በማሳለጥ የአርጎባና የአፋር ነጋዴዎች (በጊዜው አዳል ተብለው ነበር የሚጠሩት) ህዝቦች ያደረጉት አስተዋጽኦ ተስተካካይ አልነበረውም
Thread 21
በርበራና ታጁራ
ከ18ኛው ክፍለዘመን ጀምሮ ፣ በተለይ የአሁኑ ምስራቅ ኢትዮጵያ ክፍል ሐረር በማእከላዊ መንግስት ቁጥጥር ስር ከዋለ በሁዋላ የዛሬዋ ሶማሌላንድ 2ኛ ከተማ በርበራና በጊዜው በፈንሳይ ኩባንያ ስር የነበረው የአሁኑ ሰሜናዊ ጅቡቲ
Thread 22
..የወደብ ከተማ ታጁራ ለኢትዮጵያ የወደብ አገልግሎት መስጠት ጀመሩ። ይሁንና በታጁራ እጅግ ሞቃታማ ያየር ጠባይ የተነሳ የፈረንሳዩ ኩባንያ ንብረቱን ለጅቡቲ መንግስት በመሸጡና ከኢትዮጵያ ጋር የነበረውን ግኑኝነት በማቋረጡ..
Thread 23
..በርበራ ደግሞ ቀዝቀዝ ባለው የአየር ጠባዮ ምክንያት የነጋዴዎች ምርጫ በመሆኑ አብዛኛው ንግድ በዚያው ቀጥለ። የፈረንሳይ መንግስት ብዙም ሳይቆይ ከኩባንያው የገዛውን ታጁራን ትቶ በኤደን ባህረ ሰላጤ ለቅኝት አመቺ የሆነችውን
Thread 24
..የኦቦክ (በሁዋላ ጅቡቲ) መንደር ለመቀመጫነት ሲመርጥ ዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክ መንደሯን ለወደብነት ለመጠቀም ከፈረንሳይ መንግስት ጋር ስምምነት አደረጉ። ምንም እንኳን በተቀዛቀዘ መልኩ ቢሆንም ከሳቸው በፊት ኢትዮጵያን የመሩት
Thread 25
ዓፄ ዮሐንስ 4ኛ የኢትዮጵያን ቀድሞ በምጽዋ ወደብ የመጠቀምን ሁኔታ ለማመቻቸት ቢሞክሩምና የጦር አዛዣቸውን ራስ አሉን አካባቢውን እንዲቆጣጠሩ ደጋግመው ቢልኩና አንዳንድ የንግድ እንቅስቃሴዎች ቢደረጉም በምጽዋ በኩል በእሳቸው ዘመን
Thread 26
..በምጽዋ በኩል ግብጾች ፣ ደርቡሾችና ኢጣልያኖች ኢትዮጵያን ለመወረር በሚያደርጉት ሙከራ እንደ በር የሚጠቀሙበት ስፍራ በ መሆኑ እነሱን ለመመከት ፍልሚያ የሚደረግበት የብሔራዊ ስጋት ምንጭ የነበረ ስፍራ ነበር።
Thread 27
ዳግማዊ ምኒሊክ በኢትዮጵያ የወድብ አጠቃቀም ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከፈረንሳይ ጋር ባደረጉት ስምምነት የቀድሞዋን ኦቦክ መንደር ሁዋላ ጅቡቲ የተሰኘችውን በሚገባ ተጠቀሙባት። የኢትዮጵያ ዋና ወደብ በመሆኗም የባቡር መስመር ሳይቀር
Thread 28
..አስገነቡ። ዳግማዊ ምኒሊክ በፈረንሳይ ነጋዳዎች ዘንድ "ለንግድ ስራ የተመቹ ዘመናዊ አፍሪካዊ መሪ ናቸው" ብለው ያስቧቸው ነበር። ታዋቂነታቸው እስከ ዛሬ ዘልቆ በጀቡቲ መሐል ከተማ "ምኒሊክ ሆቴል" የሚባል ቆየት ያለ ህንጻ አለ
Thread 29
ጋምቤላ ወደብ
..ዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክ የደቡብንና ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያን ወደ ማእከላዊ መንግስት ሲያጠቃልሉ በባሮ ወንዝ ላይ ያለ የእቃ ማራገፍያ ስፍራ በጊዜው ሱዳንን ይገዙ የነበሩት እንግሊዞች ሲጠቀሙበት አስተዋሉ።
Thread 30
..ጠቀሜታውን በፍጥነት የተገነዘቡት ዓፄ ምኒሊክ ቦታው የኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ መሆኑን ለእንግሊዞቹ አስረግጠው ፣ ለአገልግሎቱ ክፍያ ጠይቀው ተቀበሉ። ይሁንና ከቦታው ርቀት የተነሳና ከዋና ወደብ 1366 ኪሎ ሜትር በመራቁ ከእንግሊዞቹ
Thread 31
..የአገልግሎት ቀረጥ ከመሰብሰብ ባሻገር እምብዛም ለኢትዮጵያ የውጭ ንግድ አልተጠቀሙበትም። ይሁንና የጅማውን ንጉስ አባ ጅፋርን በቅርብ እንዲቆጣጠሩትና የሚጠቀሙበትም ነገር ካለ እንዲጠቀሙ ሀላፊነቱን ሰጧቸው።
Thread 32
አባ ጅፋር ቡና የዝሆን ጥርስ እና የዱር እንስሳት ቆዳ በዚህ ወደብ ተጠቅመው ለእንግሊዞቹ በመሸጥ ከፍተኛ ገቢ ያገኙ ነበር። ከዚሁ የተገኘውንም ሀብት ለራሳቸው የሚሆነውን አስቀርተው ወደ አዲስ አበባ ለዳግማዊ ምኒሊክ ይልኩ ነበር።
Thread 33
ነገር ከትንሽ ቆይታ በሁዋላ እንግሊዞቹ አባ ጅፋርን በዚሁ ወደብ ባርያ ለመሸጥ ይጠቀሙበታል ብለው ስለከሰሱዋቸውና ዐፄ ምኒሊክ በዚህ እጅግ ተቆጥተው በወደቡ እንዳይጠቀሙ ከልክለዋቸው ነበር። ነገር ግን ከዓፄ ምኒሊክ ህልፈት በሁዋላ
Thread 34
ልጃቸው ኢያሱ 4ኛ ሲተኩ የተከለከሉቱን የወደብ ንግድ ለአባ ጅፋር መልሰው ፈቀዱላቸው። ይህ በእንዲህ ኢጣልያ ኢትዮጵያን እስክትወር ቆይቶ ሙሶሎኒ በጊዜው ሱዳንን ከምታስተዳድረው እንግሊዝ ጋር በነበረው መቃቃር ይህ ወደብ ምንም ጥቅም
Thread 35
እንዳይውል ተከለከለ። ነጻነትም ከተመለሰም በሁዋላ ወደቡ እንደ ቀረጥ ጣቢያ ሲያገለግል ከቆየ በሁዋላ ከጥቅም ውጭ ሆኖ ቆይቶ ወታደራዊው መንግስት ደርግ ለደቡብ ሱዳን አማጽያን መሳርያ ለማስታጥቅ ይጠቀምበታል ተብሎ በአለምአቀፍ...
Thread 36
..ማህበረሰብና አንዳንድ አረብ ሀገራት ክስ በመብዛቱ በ1983 እንደ አውራፓውያን አቆጣጠር ሙሉ በሙሉ ተዘጋ። በኢህአዴግ አስተዳደር ዘመን እንደገና አገልግሎት እንዲሰጥ የተደረገ አነስተኛ ጥረት ቢኖርም አሁንም ካገልግሎት ውጪ ነው።
Thread 37
የአሰብ ወደብ
አሰብ በደቡባዊ ቀይ ባህር ጫፍ የሚገኝ ቀደም ባሉት ዘመናት እምብዛም በወደብነቱ የማይታወቅ፣ ነገር ግን በጣም ሰፊና በተንጣለለ የባህር ዳርቻ የሚገኝ ወደብ ነው። ከሳምንታት በፊት በጻፍኩት ቅጥልጥል ይህ ቦታ በኢትዬጵያዊው..
Thread 38
አዳል ሱልጣን ይተዳደር የነበረ የአፋር የአርጎባ ህዝቦች መኖርያ ስፍራዎች አንዱ ነው። አፋሮች ይህንን ቦታ ከባህር ማዶ ካሉት የየመን ሐድራሙት ጎሳዎች ጋር የንግድ ልውውጥ የሚያደርጉበት ስፍራ ነበር። ቦታው እጅግ ሞቃታማና ለኑሮ የማይመች
Thread 39
..በመሆኑ ነጋዴዎች እምብዛም ለንግድ ስራ አይመርጡትም። እስከ 18ኛው ክፍለዘመን አጋማሽ ድረስ ብዙ አልፎ ሂያጆች በጽሁፋቸው ጠቀስ ከማድረጋቸው በቀር አብዛኛውን ጊዜ የዚህ ቦታ ታሪክ የሚነሳው ከአፋር ህዝቦችና አዳል ሱልጣኔት ጋር ተያይዞ
Thread 40
ብቻ ነው። የአሰብ ነገር መጉላት የጀመረው በ1830 እራሱን የካቶሊክ ቄስ ነኝ ብሎ የሚጠራ በሁዋላ ግን ብዙዎች ካህንነቱን የሚጠራጠሩት ጁሰፔ ሳፔቶ የተባለ ኢጣልያዊ ባካባቢውና በሰሜን ኢትዮጵያ ከመጣ ጀምሮ ነው።
Thread 41
ሳፔቶ ከመጣበት የ"ቅስና" ስራ ውጪ ለተለያዮ የኢጣልያ ኩባንያዎች እንደ ወኪል ሆኖ መሬት በመግዛት ተጠምዶ ነበር። በዚህም መሰረት ነበር በጊዜው የአዳል (አፋር) ስልጣን ከነበሩት ስልጣን ኢብራሒም አሰብንና አካባቢውን የገዛው።
Thread 42
ምንም እንኳን የዚህ ግዢ አፈጻጸምና መፈጸሙም እራሱ በተለያዩ የታሪክ ጸሐፊዎች አወዛጋቢ ቢሆንም ፣ የኢጣልያ መንግስት ለሩባቲኖ የእቃ ጫኝ ኩባንያ (Rubattino shipping company) የ6ሺ ማርያቴሬዛ ሽያጭ አጸደቀ።
Thread 43
ቦታው ለወደብነት ያልተዘጋጀና ለኑሮ አስቸጋሪ በመሆኑ ሩባቲኖ የተጥቀመበት ለከሰል ማራገፈያና ማከፋፈያነት ብቻ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ወደ አካባቢው የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች የመስፈንጠር ህልም ለነበራት ኢጣልያ ኩባንያው ቦታውን ሸጦ
Thread 44
ሄደ። ኢጣልያ ባካባቢው አነስተኛ የጦር ሀይል ከማስፈር በስተቀር እምብዛም በወደብነት ይህንን ቦታ እስከ ሁለተኛው የአለም ጦርነት ዋዜማ ድረስ ተጠቅማበት አታውቅም። ኢጣልያ ኢትዮጵያን ስትወር ግን ሙሶሎኒ ወደቡን መጠነኛ ጥገና አድርጎ
Thread 45
የጦር መሳርያ ለማስገባት ተጠቅሞበታል።
ኢጣልያ በጦርነት ተሸንፋ ከኢትዮጵያና የዛሬዋ ኤርትራ ስትባረርና እንግሊዞች ኤርትራን በሞግዚትነት ሲያስተዳድሩ ፣ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስለ ኤርትራ የወደፊት እጣ ፈንታ ካቀረቡት ሀሳብ
Thread 46
አንዱ አሰበንና የኤርትራን ደገኛ ክፍል ለኢትዬጵያ አስቀርቶ የኤርትራን ቆለኛ ክፍል ከሱዳን መቀላቀል ነበር። ሆኖም ነጻነት ፈላጊዎቹ የኤርትራ ቆለኛ ፖለቲከኞችም ሆኑ ከኢትዮጵያ ጋር ፌዴሬሽን ወይም አንድነት ፈላጊዎች ደገኛ ኤርትራዊያን
Thread 47
እና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ ኤርትራን የመከፋፈሉን ሀሳብ እጅግ አድርገው ስለተቃወሙት ሀሳቡ ውድቅ ሆኖ ቀረ። ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ስትቀላቀል ፣ ቀዳማዊ ሀይለስላሴ "የወደብ አስተዳደር መስርያ ቤት"
Thread 48
በሚል ተቋም አቋቁመው አሰብ ወደብን የወደብ ቁመና እንዲይዝ ስራው ተጀመረ። ይሁንና 90 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ የወደብ አገልግሎት ይከናወን የነበረው በምጽዋ ወደብ ነበር። ምጽዋ ኢጣያዊያን ለራሳቸው የቅኝ ግዛት ጥቅም አሳምረው..
Thread 49
የሰሩት ወደብ በመሆኑ እነሱ ትተውት የሄዱት መሰረተ ልማት የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ ኢትዮጵያ የባህር ሀይሏንም በዚያ አቋቋመች። ይሁንና አሰብም ቢሆን መጠነኛ መሻሻል ዘመናዊ አስተዳደርና የንግድ እንቅስቃሴ ማየት ጀምሮ ነበር።
Thread 50
የአሰብ መሰረተ ልማት እጅግ በተሻለ መልኩ የተገነባውና የወደብ ከተማነቱ የጎላው በወታደራዊው ደርግ መንግስት ነበር። ምጽዋ በጊዜው አማጺ በነበረው ሻእቢያ ለጥቃት የተጋለጠ በመሆኑ አሰብ ከአማራጭ ወደብነት አልፎ ወደ ዋና ወደብነት..
Thread 51
..እየተሸጋገረ ነበር። በደርግ መንግስት ዘመን አሰብ ዘመናዊ አውሮፕላን ማረፍያ፣ መንገዶች እና ዘመናዊ መኖርያ ቤቶች ተሰሩላት። በቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዘመን ስራ ጀምሮ የነበረው በሶቭየት ህብረት እርዳታ የተገነባው ነዳጅ ማጣርያ ስራውን
Thread 52
አጠናክሮ ቀጥሎ ድፍድፍ ነዳጅ እያጣራ ወደ መሀል ሀገር ይልክ ነበር። አሰብ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ከመሀል ሀገር ሄደው የሚኖሩበትና የአማርኛ ቋንቋ እንደዋነኛ መግባቢያ የሚነገርባት ሞቅ ያለች ሆና ነበር።
በ1983 ኢህአዴግ አዲስ አበባን
Thread 53
ሲቆጣጠር በአሰብ ቁጥሩ ቀላል የማይባል የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰራዊት ሰፍሮ ነበር። ይሁንና የዚያን ጊዜው የሽግግር መንግስት አሰብን የኤርትራ ሉዐላዊ መሬት ነው የሚል ግትር አቋም በመያዙና የተለየ ሀሳብ ያላቸውን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ...
Thread 54
ጦርነት ፈላጊ ጸረ ሰላም በሚል በማግለሉ በጊዜው በአሰብ ይኖሩ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን አስመራን ከተቆጣጠረ ከሳምንታት በሁዋላ አሰብ በዘለቀው የሻእቢያ ጦር አሳዛኝ እንግልት ደርሶባቸው ተባረሩ
Thread 55
እነዚሁ ዜጎች ለበርካታ ወራት ከላስቲክና ከጨርቅ በተሰራ የጎዳና መጠለያ በደሴና በአዲስ አበባ ጃን ሜዳ ሰፍረውን አሳዛኝ ኑሮ ይገፉ እንደነበር ከቶ የሚረሳ አይደለም። ይህንን ዛሬም ድረስ በህይወት ያሉ ወይም ልጆቻቸው ያስታውሱታል።
Thread 56
በአሁኑ ወቅት አሰብ ምንም አይነት የወደብ አገልግሎት የማይሰጥ፣ ፈጽሞ የንግድ እንቅስቃሴ የማይታይበት ፈረንጆች የመናፍስት ከተማ (Ghost City) የሚሉት እንደሆነ ይነገረል።
Thread 57
በቅርብ ጊዜ የኤርትራ መንግስት ለአረብ ኤምሬት የጦር አውሮፕላኖች የመንን ለማጥቃት ለሚያደርጉት ድብደባ እንዲጠቀሙበት እንደሰጣቸው ይነገራል። አሰብ ብቻ ሳይሆን የኤርትራም ዋና ወደብ ምጽዋ ይሄ ነው የሚባል የወደብ ስራ የማይታይበት
Thread 58
ቁጥሩ ከሀያ ሺ ያነሰ ነዋሪ ብቻ ያለበት ፣ እንደ ስልታዊ ቦታነቱ እንኳን ለአካባቢው ሀገራት እራሷን ኤርትራም ያልጠቀመበት ሁኔታ ነው ያለው። ኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላማዊ ግኑኝነት ፈጥረዋል ከተባለ ሁለት አመታት ቢያልፉም
Thread 59
ከኤርትራው ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈውርቂና ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንደ ወግ ቀጂ በሁለቱ ሀገራት ዋና ከተሞች መካከል መመላለስ እንጂ እነዚህ ወደቦች ሊያመጡ በሚችሉት ፋይዳ ላይ እየተደረገ ያለ አንዳችም ነገር የለም
Thread 60
ይህ ቅጥልጥል እጅግ በመርዘሙ ይቅርታ እየጠይኩ ፣ አስተያየት ሰጪ ኢትዮጵያዊያንም ሆነ ኤርትራዊያን ሀሳባችሁን በጨዋነት ከመግለጽ በቀር ከግላዊ ስድብ ዘረኛ አስተያየት እንድትቆጠቡ አጥብቄ አሳስባለሁ።
You can follow @Natberh.
Tip: mention @twtextapp on a Twitter thread with the keyword “unroll” to get a link to it.

Latest Threads Unrolled: